by
ይህን የግል አስተያየት እንድከትብ ያነሳሳኝ ጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. በሪፖርተር ዕትም ላይ የሠፈረውን ርዕሰ አንቀጽ መመልከቴ ነው፡፡ ‹‹በሰላምና በምግብ ዕጦት ለሚፈተኑ ወገኖች መፍትሔ ይፈለግ!›› በሚል አገራዊ ጥሪ ላይ የተመሠረተው ይህ ወቃሽና መካሪ ሐሳብ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻችንን ተነጋግሮ ለመፍታት አለመቻላችን ቀውሱን እያባባሰ መሄዱን ክፉኛ ይኮንናል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ምድር ግጭትን በዘላቂነት ለማስቆም የሚያስችሉ በቂ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው በእኩልነት ለመቀራረብ፣ ለመነጋገርና ለመደራደር ፈቃደኛ ሆኖ መገኘት ነው…›› የሚለው ርዕሰ አንቀጹ፣ ‹‹ፈቃደኝነቱ የሚመነጨውም በመከባበር ስሜት በጋራ አገርን ለማስቀጠል ከሚኖር ፍላጎት ነው፡፡ ይህ ፍላጎት መመሥረት ያለበት ከምንም ዓይነት ዓላማ በላይ አገርን በማስቀደም ነው…›› በማለትም ያስታውሳል፡፡
በዚህ ጸሐፊ ዕይታም ቢሆን መነጋገር፣ መደማመጥና በሰጥቶ መቀበል ተከባብሮና ተቻችሎ መኖር ባለመቻሉ ጥፋት እየደረሰ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት በታሪክ ተደማምረው ከቆዩቱ ችግሮቻችን በሚመነጩ ዕሳቤዎችም ሆነ አዳዲስ ትርክቶችን በማስፋፋት በየአካባቢው ግጭቶች፣ የሰላም መደፍረሶችና ጦርነቶች በማያቋርጥ አኳኋን መቀጠላቸው አገርን ወደ ቀውስ እየገፉ ነው፡፡
ከሦስት ዓመታት በፊት በትግራይ ክልል በተነሳው ጦርነት በአጠቃላይ ሰሜን ቀጣና (አማራና አፋርን ጨምሮ) ያደረሰው ጉዳት እጅግ አሰቃቂ ከመሆኑ ባሻገር፣ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት የአገር ሀብት መብላቱ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት ጋብ ያለ ቢመስልም፣ አሁንም የጦርነት አዙሪቱ ቀጥሎ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በርካቶችን ለሕልፈተ ሕይወት እየዳረገ ነው፡፡ ለአሁኑ የአማራ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ ለመፈተሽ እሞክራለሁ፡፡
ባለፈው ሰሞን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ የአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች በተለያየ ደረጃና ጊዜ የትጥቅ ግጭት ተካሂዶባቸዋል። በተጨማሪም እነዚህ አካባቢዎችና ወረዳዎች በአንድ ወቅት በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች፣ በሌላ ወቅት ደግሞ በታጣቂው ቡድን (በተለምዶ ፋኖ በመባል የሚታወቀው) በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
የትጥቅ ግጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያና አልፎ አልፎ በአየር/ድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ ነው ያለው መግለጫው፣ በግጭቱ ዓውድ ውስጥ የአየር/ድሮን መሣሪያን ጨምሮ በከባድ መሣሪያዎች ጥቃት ሳቢያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሞትና የአካል ጉዳት የደረሰ መሆኑን፣ መኖሪያ አካባቢያቸውን ጥለው ለመሸሽ የተገደዱ ሰዎችም በርካታ መሆናቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው አስታውቋል።
ለአብነት ሲጠቀስም በሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ ‹መጥተህ ብላ› ከተማ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈጸመ የድሮን ጥቃት የአንድ ዓመት ከሰባት ወር ሕፃንን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ያለው ኢሰመኮ በደብረ ማርቆስ ከተማ ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ቢያንስ ስምንት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንም ነው ያረጋገጠው። በተመሳሳይ በደንበጫ ከተማ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በከባድ መሣሪያ ድብደባ ምክንያት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ደርሷል ብሏል። ኮሚሽኑ እነዚህን መረጃዎች ያገኘው የአካባቢውን ነዋሪዎችና የዓይን ምስክሮችን በማነጋገር መሆኑን አስታውሶ፣ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ጥቃትን አልያም ግጭትን በመሸሽ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ መቻሉንም በመግለጫው አካቷል። በምንጃር ወረዳ ውስጥ የአውራ ጎዳና ጎጥ ነዋሪዎች ከመስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከቀዬአቸው ተፈናቀለው ቢያንስ 3‚000 ያህሉ አሞራ ቤቴ ቀበሌ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤትና ክፍት ሜዳ ላይ (በዛፍ ሥር) ተጠልለው የሚገኙ መሆናቸውን፣ ሌሎች ቁጥራቸው ያልታወቀ መተሐራና አዋሽን ጨምሮ ወደ የተለያዩ አካባቢዎች መፈናቀላቸው ለማኅበራዊ ቀውሱ እንደ ማሳያም ጠቅሶታል።
ለተፈናቃዮች የተወሰነ ድጋፍ በማኅበረሰቡና በአንድ ተራድኦ ድርጅት የተደረገ ቢሆንም፣ በቂ ባለመሆኑ በአሳሳቢ ሁኔታ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል ያለው ኢሰመኮ የነዋሪዎችን መፈናቀል ተከትሎ ሰብላቸው እንደ ወደመ፣ ንብረታቸው እንደ ተዘረፈ፣ የቤቶቻቸው ጣሪያና በር እየተነቀለ እንደ ተወሰደ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቤቶቻቸውን ከአጎራባች ክልል በመጡ ኃይሎች በኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ጭምር ማፍረስ እንደ ተጀመረ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና የመንግሥት ኃላፊዎች አስረድተዋል ብሏል። በመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባላት የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች አሁንም መቀጠላቸውን ኢሰመኮ ተዓማኒ መረጃዎችን እየተቀበለ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ ግጭት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሰዓት ዕላፊ ገደብ፣ በኔትወርክና በስልክ መቋረጥና በምርቶች መንቀሳቀስ አለመቻል ሳቢያ የብዙዎች ሕይወት እየተመሰቃቀለ መሆኑንም አስታውቋል፡፡ በእርግጥ አንደ የአሜሪካ ድምፅ፣ የጀርመን ሬዲዮና ቢቢሲ አማርኛ ላይ እየተስተናገዱ ያሉ የሕዝብ አስተያየቶች እንደሚያስረዱት በክልሉ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በከባድ መሣሪያና በአየር ድብደባ መታገዙ ብቻ ሳይሆን፣ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለም ነው።